መሰልጠን ወይስ መሰይጠን?
በቅርቡ በጎንደር ከተማ በአንድ ሆቴል የእንግዳ መቀበያ ክፍል አጠገብ ካሉት ወንበሮች በአንደኛው ላይ ቁጭ ብዬ ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ የጀመረውን የቶትንሃምና የሳውዝአምፕተን ጨዋታ በቴሌቪዥን እከታተላለሁ።
ሆቴሉ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በምቾት የምታዩበት ሆቴል ብቻ ሳይሆን ጥንታዊቷን የጎንደር ከተማ ቁልጭ አድርጎ ከሚያሳየው ተራራ ላይ ተጠግቶ የተሰራ ነው። ጨዋታውን የሚያስተላልፈው ጋዜጠኛ/ኮሜንታተር/ ድምጽ ሞቅ ሲል ወደ ቴሌቪዥኑ አፈጣለሁ ። ድምጹ ቀነስ ሲል የጎንደርን ውበት፣ ወጣ ገባ ተራራዎች፣ ጥንታዊነቷን የሚመሰክሩ ቅርሶችና አብያተ ክርስትያናትን በቅርብ ርቀት እቃኛለሁ።
በከተማዋ መንገዶች ሲጓዙ ማየት የማይችሏቸውን የውስጣ ለውስጥ መንገዶች፣ ሰፈሮች፣ ተቋማት፣ ዛፎች፣ የሰውና የመኪና እንቅስቃሴ ሁሉ በሆቴሉ ላይ ቁጭ ብለው በአንድ ሞሰብ እንደቀረበ ምግብ በቀላሉ ማየት ይችላሉ። የራቀው ቀርቦ፣ ተራራ ታች ወርዶ፣ ጉድጓዳ ውስጥ ያለው ወጥቶ…ቁልጭ ብሎ ይተያል።
ፒያሳ አካባቢ ያሉት በጣሊያን ወረራ የተገነቡትና በቅርስነት የተያዙት ባለ ሽሮ ቀለም ህንጻዎች፣ የፋሲል ግንቦች፣ ዘመኑ ያፈራቸው ትላልቅ ሆቴሎች፣ ተራራ ላይ የከተመው የጎንደር ዩንቨርሲቲ ህንጻዎች….ከርቀት ጎልተው የሚታዩ ናቸው። ጃን ተከል ዋርካን ሆቴሉ ላይ ሆኜ ማየቴን እርግጠኛ ባልሆንም ጥንታውያን ዛፎችም የከተማዋ ውበት መሆናቸውን ማየት ይቻላል።
እንደ እኔ ላለ የእግር ኳስ አፍቃሪ ተመልካች ከጦፈው የቶትንሃምና ሳውዝ አምፕተን ጨዋታ ይልቅ የጎንደር ከተማን ደግሞ ደጋግሞ ማየት፣ መመልከት፣ መገንዘብና መረዳት ያለሁበት ቦታ ምን ያህል ሳቢ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም።
ልቤም፣ አይኔም፣ ቀልቤም… ወደ ከተማዋ ዙሯል። ብዙ የሚነገርላት፣ የምትመረመር፣ የምትገለጥ፣ የምትነበብ… ሁልጊዜም የእውቀት ምንጭ ከተማ ጎንደር ላይ ነው ያለሁት። እንደ ነገርኳችሁ ኮሜንታተሩ ኦ! …ጎል!.. እያለ ሲጮህ ኮሽ የሚል ድምጽ እንደሰማ መንገደኛ ብትት ብዬ ወደ ኳሱ አፈጣለሁ። ቀዝቀዝ ሲል አንገቴ እስኪጠመዘዝ ድረስ ከተማዋን ዳር እስከ ዳር እቃኛለሁ።
አሁን ደግሞ የከተማዋን ውበት፣ ጥንታዊነትና ማራኪት… የቶትንሃምና ሳውዝ አምፕተን ጨዋታ የሚያስረሳ አንድ ክስተት ተመለከትኩ ። ሆቴሉ ከታች ሁለት ፎቅ ያህል ወደ ላይ እንደተገነባ ላዩ ላይ ሰው ሰራሽ ሳር የለበሰ ስታዲየም የሚመስል መዝናኛ አለው። እንደገና ወደ ላይ እግር የሚያደክሙ ደረጃዎችን ወጥተው ነው ዋናውን የሆቴሉ ክፍል የሚያገኙት።
ከዚህ ሳር ከለበሰው ሜዳ ከፍ ብሎ ደግሞ ወጣቶች፣ ፍቅረኛሞች፣ እንግዶች፣ ጎብኚዎች… በቡድን በቡድን ወይም በተናጠል ሆነው ጠረጴዛ ይዘው ቢፈልጉ ኢንተርኔት የሚጠቀሙበት፣ ለስላሳ፣ ቢራ፣ ሻይ ቡና… ፉት እያሉ የሚዝናኑባቸው ቦታዎች አሉ። ካልፈለጉም እንደእኔ የከተማዋን ውበት እያዩ የሚያደንቁበት፣ የውስጥ ስሜትዎን የሚያዳምጡበት፣ የሚያሰላስሉበት…ምቹ መቀመጫዎች ያሉት ቦታ ነው።
ከዚህ ቦታ በአንደኛው ላይ ሁለት ህጻናትን የያዙ አምስት ያህል ሰዎች በፌስታልና በካርቶን የታጨቁ ቁሳቁሶችን ይዘው በመምጣት ቁጭ ሲሉ ቀልቤም እነሱ ጋ ሆኖ አረፈ። አስተናጋጆችም ምን እንደሚፈልጉ ከተነጋገሩ በኋላ ተጨማሪ ጠረጴዛዎችን፣ ወንበሮችን እያስተካከሉ መደርደርና እንግዶችን ማስቀመጡን ተያያዙት። በእውነት የአገራችን ትላልቅ ሆቴሎች መስተንግዶ እየተሻሻለ መምጣቱን በአስተናጋጆች መጣደፍ አረጋግጫለሁ።
ስልክ እሷም ጋ፣ እሱም ጋ ይደወላል። ተጨማሪ እንግዶች ይመጣሉ፤ በኢትዮጵያዊነት ባህል ቁመው ይቀበላሉ፤ ተሳስመው፣ ተቀላልደው፣ ተጨዋውተው…ተሳስቀው… ወንበር ይዘው እንዲቀመጡ ይጋበዛሉ፣ እነሱም ይቀመጣሉ። ሌሎችም ይመጣሉ እንደዛው ያደርጋሉ። ህጻናትና የከተማ ሰዎች ብቻ ሳይሆን የገጠር አለባበስ የለበሱ አባቶችና እናቶችም አሉ። አያት የሚሆኑ ሽማግሌዎችም ይገኛሉ።
ሰርግ ነው? ወይስ መተጫጨት? አሊያስ ጎንደር በርካታ ዲያስፖራ ያለባት በመሆኑ ከውጭ የመጣ ዘመድ እየተጠባበቁ?፤ የቤተሰብ መዝናኛ ፕሮግራም? ወይስ ምንድን ነው ፕሮግራማቸው?… እኔ ማሰብ ጀመርኩ። ጊዜው እየረዘመና እየመሸ ሲሄድ የእኔም ማሰብ፣ ማምሰልሰል… ተጠናክሮ ቀጥሏል። ህጻናት ይቦርቃሉ፣ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ይሳሳቃሉ፣ በሰል ያሉት ሰዎች ደግሞ ይመካከራሉ፣ ይወያያሉ… ፊታቸው የሁሉም የፈካ በመሆኑ የምወደውን የእግር ኳስ ጨዋታና የጎንደር ከተማን ውበት ማየት ትቼ እነሱ ላይ እንዳፈጥ አስገድዶኛል።
አስተናጋጆች ተጠርተው ሄዱና መድረኩን ማስዋብ ጀመሩ። ፌስታሎች ተከፍተው ሰንሰለት የመሰሉ የተለያየ ቀለማት ያላቸው መብራቶች ተሰቀሉ ። ከሶኬት ጋር ተገናኝተው ብልጭ ድርግም እያሉ ቀይ፣ ቢጫ፣ ሰማያዊ፣ አረንጓዴ…ቀለሞችን መርጨት ጀምረዋል፤ ፊኛዎች ተወጥረው ተንጠልጥለው በነፋሱ ይወዛወዛሉ፣ በተለያየ ከለር የተዋበ ካርቶን ወጥቶ ፊት ለፊት ካለው ጠረጵዛ ላይ ተቀመጠ ። ለእያንዳንዱ ሰውም ለስላሳ መጠጦች ታደሉ።
አሁን ጉዳዩን ማረጋገጥ ባልችልም መገመት ከማያዳግተኝ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። የሶስት ዓመቷን ህጻን የተለያየ ልብስ በማልበስ ማስዋብ ይዘዋል። ጫማዋ፣ ቀሚሷ፣ ሱሪዋ… ተቀይሯል። አሻንጉሊት የመሰሉ ነገሮች የተንጠለጠሉበት ኮፍያ ከራሷ ላይ ተደፋላት። ካርቶኑ ተከፈተ። ስም ተጽፎበታል ለማንበብ ግን ትንሽ ራቅ በማለቱ ማንበብ አልቻልኩም። በግምት የሶስት ዓመቷ ህጻን ቢላዋ ተሰጥቷት ከካርቶኑ ፊት ለፊት ወንበር ላይ እንድትቆም ተደረገች።
መልካም ልደት ለ… የሚለው የፈረንጆች መዝሙር መዘመር ተጀመረ። ሻማውን ለኮሰች፣ ኬኩን ቆረሰች… የቤተሰቡ እልልታና ጨዋታ ደመቀ። ፎቶ ግራፍ የሚያነሳው ወጣት ከፊት ለፊት፣ ከጎን፣ ከኋላ…እየሆነ ሲፈልግ አጎንብሶ፣ ሲያሻው ቁጭ ብሎ፣ ሲደክመው ቆሞ..ፎቶ ግራፍ ያነሳል። ደጋግሞ ያነሳል። ጨዋታው ደምቋል።
እኔን ያስደነገጠኝና ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ድርጊት የተፈጸመው ከዚህ በኋላ ነው። ዝማሬው፣ እልልታው፣ ጨዋታው በደመቀበት ሁኔታ ላይ አንድ ነገር ተከሰተ። ነገሩ እንዲህ ነው። ያች የሶስት ዓመት ህጻን ወዳለችበት ሌላ ተመሳሳይ እድሜ ያለው ወንድ ህጻን አቅፈው ወስደው ከጎን ካለው ወንበር እንዲቆም አደረጉት። እሷ ወደ እሱ፣ እሱም ወደ እሷ እንዲዞሩ አስተባበሪዋ አዘዘች። ህጻናቱም እንደታዘዙት አደረጉ።
እሱም ወደ እሷ፤ እሷም ወደ እሱ ዙረው ፊት ለፊት ይተያያሉ። ሁሉም ታዳሚ ያጨበጭባል፣ እጁን ያወዛውዛል፣ መልካም ልደት ለ… እያለ ይዘምራል። ተሳሳሙ ተባሉ ህጻናቱ። ከንፈር ለከንፈር እንዲሳሳሙ አዘዟቸው። ህጻናቱም አደረጉት ። ፎቶ ግራፍ የሚያነሳውን ወጣት ፊት ለፊት ሆነህ አንሳ እያሉ ይጮሁበታል። እሱም ብልጭ ብልጭ ያደርጋል። ድገሙ፣ ድገሙ… እያሉ ደጋግመው ከንፈር ለከንፈር ያሳስሟቸዋል።
ይህንን ድርጊት ሳይ በእነዚህ ህጻናት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሆኖ ተሰማኝ። በተረት ተረት የምሰማው ልጅህን ለልጄ ጋብቻ ነው? ወይስ…ምንድን ነው?። የወሎው ግጥግጥ፣ የጎጃሙ ማደጎ… የህጸናት ጋብቻ እየቀረ በመጣበት ዘመን በውቧና ስልጡኗ ከተማ ጎንደር ያየሁት እውነት ልደት አከባበር? ወይስ ጋብቻ? ምላሹን ማግኘት አልቻልኩም።
የልደት አከባበር ቢሆንስ እንዴት? ምንም የማታውቅ የሶስት ዓመት ህጻን ከአቻዋ ጋር እንድትሳሳም ይደረጋል። ለምንስ ይህን ለማድረግ አነሳሳቸው?። እነዚህ ህጻናት በህዝብ ፊት ያውም እየተዘመረላቸው፣ አየተጨበጨበላቸው፣ እልልታ እየቀለጠላቸው… መሳሳም ከጀመሩ ነገ ከነገ ወዲያ በየመንገዱ፣ አካባቢው…የሚያገኙትን ህጻናት ከንፈር ከመምጠጥ ወደ ኋላ አይሉም።
ምክንያቱም ቤተሰቦቻቸው ህዝብ በተሰበሰበት ያደረጉትና የተፈቀደላቸው በመሆኑ ህጻን እንኳን አድርጎ ያየውን ሁሉ ልሞክር፣ የተሰማውን ሁሉ ልናገር፣ የተነካውን ሁሉ ልንካ፣ የተረገጠውን ሁሉ ልርገጥ… የሚል ተፈጥሯዊ ባህሪ አላቸው።
የተባበሩት መንግስታት እ.ኤ.አ 1959 ባወጣው የህጻናት መብት ድንጋጌ ህጻናት በአካል፣ በአእምሮና በመንፈስ ጎልብተው እንዲያድጉ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና መንግስታት መስራት መስራት አለባቸው ይላል። ዝቅ ብሎም ደህንነታቸው፣ ጤንነታቸው… እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።
የሶስት ዓመት ህጻናትን ከንፈር ለከንፈር ማሳሳም በአስተደጋገቻው ላይ፣ በስነ ልቦናቸውና በመንፈሳቸው ላይ ምን አይነት ተጽእኖ እንደሚኖረው መገመት አያዳግትም። በመንፈስ የህጻናት አእምሮ የሚጎለብተው ከማህበረሰቡ ጋር የተጣጣመ ባህል፣ ክዋኔ፣ ድርጊት…አውቀው፣ አይተውና ተግብረው ሲያድጉ ነው።
እነዚህ ህጻናት መንገድ ላይ ሌላ ህጻን አግኝተው ተደጋጋሚ ድርጊት ሲፈጽሙ ቢታዩ ሊደርስባቸው የሚችለውን ዘለፋ፣ ወቀሳና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሞራል ውድቀት ታስቦ ይሆን?
ህጻናት ሁሉንም ለማወቅ ስለሚጓጉ ይጠይቃሉ… ይጠይቃሉ… ከተመለሰላቸው ሌላ ጥያቄ ይፈጥራሉ። አላውቅም ብሎ መልስ አይፈልጉም ለምን አታውቅም? የሚል ጥያቄ ይከተላል። ታዲያ አንዲህ ባለ የህጻን አእምሮ እርስ በእርሳቸው ያውም እያጨበጨቡ፣ እየዘመሩ እንዲሳሳሙ መፍቀድ ከአገራችን ባህል፣ ወግ፣ ሃይማኖት…. ጋር እንዴት ይታያል።
ነገሩ በጣም ስለገረመኝ ከጎኔ ተቀምጦ ኳስ ሲያይ የነበረውን አነድ ሰው እንዲህ ስል ጠየኩት። አየኋቸው እነዚህን ህጻናት እንዴት እንደሚያደርጓቸው አልኩት። ዘወር አለና የሚገርም አሳፋሪ ድርጊት ነው አለኝ።
አንተ ከሁለት ዓመት በላይ ሆላንድ ኖረሃል እንዴት የአውሮፓ ባህል የህጻናት ልደት ሲከበር እንደዚህ ያለ ነገር ይፈጸማል እንዴ ብዬ ጠየኩት። አይደረግም ታይቶም አይታወቅ፣ 13 ፣ 14 እና ከዚያ በላይ እድሜ ሲሆኑ ሁሉንም ነገር እያወቁ እንዲሄዱ ከጓደኞቻቸው ጋር የመቀራረብ፣ የመተዋወቅና የማውራት ባህል ስላላቸው አይከለከሉም። በህጻንነት ግን አይደረግም አለኝ።
ታዲያ ጎንደር የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት፣ የሃይማኖት አገር፣ የአኩሪ ባህል ባለቤት…ስትሆን እንደዚህ አይነት መሰልጠን አይሉት መሰይጠን ድርጊት ከዬት ተገኜ አልኩኝ በልቤ። ምን አልባት ይህ እንግዳ የሆነብኝ ለእኔ ብቻ እንዳይሆን ሌሎች ሰዎች ማነጋገር ጀመርኩ።
ህጻናት ከሁለት እስከ ስድስት ዓመታቸው ድረስ የሚያዩት፣ የሚከውኑት፣ የሚሰሙት… የልጆቹ ዘላቂ ባህሪን የሚወስን እንደሚሆን የገለጹልኝ በባህርዳር ዩንቨርሲቲ የሳይኮሎጅ ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር አቶ ፈይሳ ሙሊሳ ናቸው።
እንደ ምሁሩ ገለጻ ሶስት አይነት ቤተሰብ አለ። አምባ ገነን፣ ልቅና ዴሞክራሲያዊ ቤተሰብ ናቸው። አምባ ገነን ቤተሰብ ሁልጊዜም ልጆችን በመቅጣትና በመገሰጽ ተሸማቀው እንዲያድጉ ያደርጋል። ልቅ የሚባለው ደግሞ ልጆች ምንም ያድርጉ አያድርጉ፣ ያጥፉም ያልሙም፣ ምን እንደሚደሚሰሩና ምን መስራት እንዳለባቸው ክትትል የማያደርግ ከነጻነት ያለፈ መብት ብቻ የሚሰጥ ነው። ሁለቱም በህጻናት አስተዳደግ ተፈላጊ አይደሉም።
ተመራጩ ዴሞክራሲያዊ ቤተሰብ ነው። ይህም በህጻናት አስተዳደግ ጥሩውን ነገር ከመጥፎው እየለዩ እንዲያድጉ የመወያየት፣ የመመካከርና የማስተካከል ባህልን እያጎለበተ፣ ሁሉንም በምክንያታዊነት እያስረዳና እየተረዳ ስለሚያሳድግ በዚህ አስተዳደግ ያለፉ ልጆችም በግሎቫላይዜሽን ዘመን ተወዳድረው አሸናፊ የመሆን ብቃታቸው የጎለበተ ነው። መብትና ግዴታቸውን ከታች ጀምሮ አውቀው ያድጋሉ። መብታቸውን ይጠይቃሉ፣ ለማስከበር ይታገላሉ…፣ ግዴታቸውንም አውቀው ከመፈጸም ወደ ኋላ አይሉም ብለዋል።
እኔም ከምሁሩ አባባል ህጻናት እንዲሳሳሙ የገፋፉት ቤተሰቦች ልቅ ከሚባሉት የሚመደቡ መሆናቸውን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም።
ህጻናቱም ካሁኑ የመሳሳም ሁኔታ ከለመዱ እድሜያቸው ለአቅመ አዳምና ሄዋን ሳይደርስ የመድፈርና የመደፈር እድል ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ነው የተናገሩት። አክሽን ፊልም እያየ ያደገ ህጻን ተደባዳቢና በስርቆት የሚሰማራ ይሆናል። ሱሰኛ ቤተሰብ ያለው ህጻን ለጫት፣ ሲጋራና ሌሎች ሱሶች የመጋለጥ እድሉ የሰፋ ነው። ጠጭ ቤተሰብ ያለውም ቀድሞ መጠጥ በመጠጣት ሰካራም ይሆናል። ቤተሰብና ማህብረሰብ ለህጻነቱ ዘላቂ ህይወት መሰረት ነው ብለዋል።
ይህ ነገር ፍቅር የሚባለውን የተቃራኒ ጾታ ስጦታ እንዳያጠፋው ሰጋሁ። ፍቅር ማለት ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ጉብሎችና ኮረዳዎች በመነፋፈቅ፣ በመጓጓት፣ በድብቅ…የሚፈጽሙት በጎ ተግባር ነው። እንዳሁኑ በየመንገዱ፣ በየአደባባዩ፣ በየታክሲ ወንበሩ፣ በየካፌው… እየተጓተቱ መሳሳም ሳይሆን በድብቅ የሚፈጽሙት ለራሳቸው ብቻ የተሰጠ፣ የግል ስጦታቸው በመሆኑ ነው ፍቅር የተባለው።
አሁን ያየሁት ግን እውነታኛው ፍቅር ላይ ጥላ የሚያጠላ ድርጊት በመሆኑ ሆቴሎችም በጊቢያቸው የሚካሄዱ ስነ ስርዓቶችን በመከታተል መጥፎ ድርጊቶችን ሊያስቆሙ ይገባል እላለሁ።
እንግዳው ከፍያለው / ኢዜአ/
Comments
Post a Comment