በዓለም ላይ ከሚገኙት ወደ 3000 የሚጠጉ የእባብ ዝርያዎች 600 የሚሆኑት መርዛማ ናቸው፤ የተነደፍነው በመርዛማ እባቦች መሆኑን እንዴት እንለያለን? ምንስ ማድረግ አለብን?

በዓለም ላይ ከሚገኙት ወደ 3000 የሚጠጉ የእባብ ዝርያዎች 600 የሚሆኑት መርዛማ ናቸው፤ 200 የሚሆኑት ደግሞ ለህክምና ወይም ለመድኃኒት አግልግሎት የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ መርዛማ እባቦችን ለመለየት ይሄ ነው የሚባል መንገድ ለመከተል ይከብዳል፤ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የመለያ መንገዶች የቅርብ ምልከታን የሚፈልጉ በመሆኑ ነው፤ ስለዚህ ከእባቦች ስጋትና ጥቃት ነፃ ልንሆን የምንችለው ከእነርሱ በመራቅ ነው፡፡
የአንድ መርዛማ እባብ ንድፊያ የተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ በፍጥነት ጉዳት ማድረስ ይጀምራል፤ እንደ ሳንባ፣ ልብ፣ የማዕከላዊ ነርቭ ስርዓት፣ የቀይ ደም ሕዋሶችና የጡንቻ ስርዓት ያሉት በቀጥታ ጉዳት ከሚገጥማቸው የሰውነት አካላት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም የእባብ መርዝ የነርቭ ስርዓትን የሚያጠቃ(neurotoxic)፣ በደም ሕዋሶች ላይ ጉዳት የሚያደርስ(haemotoxic)፣ ልብን የሚጎዳ(cardiotoxic) እና በጡንቻዎች ላይ እንከን የሚፈጥር(myotoxic) ተብሎ ሊከፈል ይችላል፤ በዚህ ምክንያት የሚሰጠውም የማርከሻ ሕክምና የተለያየ ነው፤ ይህ በመሆኑም በሕክምናው ስኬታማ ለመሆን በምን ዓይነት እባብ እንደተነደፍን ማወቅ አለብን፡፡
በዓለማችን ላይ በአመት ወደ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በእባብ ይነደፋሉ፤ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 100 ሺህ የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጣሉ
በዓለማችን ላይ በአመት ወደ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በእባብ ይነደፋሉ፤ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 100 ሺህ የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጣሉ፤ 5 መቶ ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ቋሚ የአካል ጉዳት ይገጥማቸዋል፤ የመርዛማ እባብ ንድፊያ ማርከሻውን ካላገኘ ለሞት የመዳረግ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ እባቦች በአማካኝ በሳምንት አንድ ጊዜ ይመገባሉ፤ ከተመገቡ በኋላ እንዲሁም ቆዳቸውን በሚሸልቱበት ጊዜ በጣም ዝግተኛ ስለሚሆኑ ሲንቀሳቀሱ አይታዩም፤ በመሆኑም ካሉበት አካባቢ ጋር ተመሳስለው ስለማይታዩ ያለማወቅ ልንረግጣቸውና ሊነድፉን ይችላሉ፤ ስለዚህ በሰርቫይቫል ሁኔታዎች ውስጥ የምንረግጥበትን ቦታ አስቀድሞ ማየት ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ፍራፍሬ ከዛፍ ላይ ለመቅጠፍ ከመሞከራችን በፊት፣ እንጨቶችን ከመሬት ስናነሳና ግብስባሶችን ስንገላልጥ ተጠንቅቀንና አስተውለን መሆን አለበት፤ ድንጋዮችን ስንፈነቅል እንዲሁም ጢሻዎችን ስንገላልጥ እንጨቶችን በመጠቀም መሆን አለበት፤ በተጨማሪም ከመኝታ እንዲሁም ልብስና ጫማ ከማድረጋችን በፊት እባቦች እንደ መጠለያ ሊጠቀሙት ስለሚችሉ ገላልጠንና አራግፈን ማረጋገጥ አለብን፡፡
መርዛማ እባብ ንድፊያን መለየት
በስዕል እንደምትመለከቱት መርዛማ ባልሆኑ እባቦች በምንነደፍበት ጊዜ፣ የተነከስንበት ቦታ ላይ ተመሳሳይ የሆነ የጥርስ ምልክት በተርታ(2) ልንመለከት እንችላለን፡፡ ነገር ግን መርዛማ በሆኑ እባቦች በምንነደፍበት ጊዜ የተነከስንበት ቦታ ላይ ተመሳሳይ ከሆኑ የጥርስ ምልክቶች በተጨማሪ ለየት ያሉ(1) የጥርስ ምልክቶችን ልንመለከት እንችላለን፤ እነዚህ ለየት ያሉ የጥርስ ምልክቶች ሁለት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት የጥርስ ምልክቶች(fangs)፣ መጠናቸው ከሌሎቹ የጥርስ ምልክቶች የሚተልቅ ነው፤ እባቡ መርዙን ወደሰውነታችን የሚጨምረው በእነዚህ ጥርሶቹ አማካኝነት ነው፡፡ በተጨማሪም በስዕሉ እንደምትመለከቱት የመርዛማ እባብ ንድፊያን ለመለየት የእባቡን የጭንቅላት ቅርፅ ልንጠቀም እንችላለን፤ የእባቡ ጭንቅላት ቅርፅ የሦሥት ማዕዘን ወይም ዳይመንድ ቅርፅ ከሆነ፣ እባቡ መርዛማ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፤ ጭንቅላቱ ልክ እንደ እንቁላል ያለ ከሆነ ደግሞ መርዛማ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
የመርዛማ እባብ ንድፊያን መለየት
በመርዛማ እባቦች ለመነደፋችን ጠቋሚ የሆኑ ሌሎች ምልክቶችንም በተጨማሪ ልንመለከት እንችላለን፤ ለምሳሌ በአፍንጫ እና በፊንጢጣ ደም መምጣት፣ ደም የተቀላቀለበት ሽንት መሽናት፣ እያደገ የሚሄድ የህመም ስሜት፣ የተነከስንበት ቦታ ላይ ማበጥ፣ ከፍተኛ ድካም፣ የሰውነት መዝለፍለፍና ለመተንፈስ መቸገር ከተነከስን በኋላ ባሉት ሁለት ሰዓታት ውስጥ ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች ናቸው፡፡ በስዕል እንደምትመለከቱት የመርዛማ እባብ ንድፊያ በሰውነታችን የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰው የጤና ችግር ምን ያክል ከባድ እንደሆነ ነው፡፡

በመርዛማ እባቦች ለመነደፋችን ጠቋሚ የሆኑ ሌሎች ምልክቶችንም በተጨማሪ ልንመለከት እንችላለን
አስታውሱ! እባቦች እንቅስቃሴ ማድረግ እስካልጀመሩ ድረስ ከአካባቢ ለይቶ ለማየት በጣም አስቸጋሪ ናቸው፤እባቦች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ብዙዎቹን ሳናስተውላቸው በቅርበት ልናልፋቸው አልፎ ተርፎም ልንረግጣቸው እንችላለን፡፡ ማንኛውንም የእባብ ንድፊያ ትኩረት ሰጥተን በፍጥነት መታከም አለብን፡፡ እባቦችየሚናደፉት እራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በሆነ ጊዜ አነስተኛ መርዛቸውን ይጠቀማሉ፤ አንዳንዴ እንደውምሲናከሱ መርዛቸውን ፈፅሞ ላይጠቀሙ ይችላሉ፤ መርዛቸውን በአብዛኛው የሚጠቀሙት ምግብ ሊሆኗቸው የሚችሉ ታዳኞች ላይ ነው፤ እባቦች በቅርብ ንድፊያ ፈፅመው ከሆነ፣ የሚኖራቸው መርዝ ስለሚሟጠጥ ንክሻቸው አደጋ ላይፈጥር ይችላል፤ ነገር ግን እነኝህ ሁኔታዎች ሊያዘናጉን አይገባም፤ እባቦችን ምንግዜም መጠንቀቅ ነውያለብን፡፡
ከዚህ በመቀጠል በእባቦች አማካኝነት ሊደርስብን ከሚችል አደጋ ቀድመው ሊከላከሉን የሚችሉ ጥቆማዎችን እንመልከት፡-
  • የምንገኘው እባብ በብዛት ሊኖርባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ከሆነ፣ እርምጃችንን ተጠንቅቀን፣ የምንረግጥበትንም ቦታ እየተመለከትን መሆን አለበት፤ በተለይ በጫካ ውስጥ፡፡
  • በዛፎች፣ በቅጠል እና በውኃ አካባቢዎችም ሊኖሩ ስለሚችሉ መጠንቀቅ አለብን፡፡
  • እባቦች አይናቸውን መክደን አይችሉም፤ ስለዚህ መተኛት አለመተኛታቸውን በማየት መለየት አይቻልም፤ እባቦችን ለመጉዳት ወይም ለመቃለድ እንዳትሞክሩ፡፡
  • የሚጠረጠሩ ቦታዎችን ለምሳሌ ከእንጨቶች ስር፣ ከድንጋይ ስርና ሌሎችም ነገሮች ውስጥ በእጃችን አገላብጠን ለማየት መሞከር የለብንም፤ ረዘም ያሉ እንጨቶችን መጠቀም አለብን፡፡
  • በሰርቫይቫል ሁኔታዎች ውስጥ እግሮቻችንን በተለይ በለሊት ወቅት ከእባቦች ጥቃት ለመከላከል አስተማማኝ ጫማ ማድረግ አለብን፡፡
  • ወድቀንም ሆነ በመንገዳችን ላይ ከእባቦች ጋር ፊት ለፊት በቅርብ ርቀት ከተጋፈጥናቸው ማድረግ ያላብን እንቅስቃሴዎችን በማስወገድ ጥለውን እንዲሄዱ እድሉን ማመቻቸት ነው፤ እባቦች ድምፅ መስማት አይችሉም፡፡
  • እባቦች ደመ ቀዝቃዛ ናቸው፤ በመሆኑም ሞቃት ገላችን ወደኛ ሊስባቸው ይችላል፤ ስለዚህ በምንተኛበት ወቅት በቂ ሽፋን ለገላችን መስጠታችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡
እባቦች እንቅስቃሴ ማድረግ እስካልጀመሩ ድረስ ከአካባቢ ለይቶ ለማየት በጣም አስቸጋሪ ናቸው

በዓለማችን ላይ መርዘኛ እባቦች የሉባቸውም የሚባሉ አገሮች ኒውዚላንድ፣ ኩባ፣ ኃይቲ፣ ጃማይካ፣ ፖርቶ ሪኮ፣ አየርላንድ፣ ፓሊኔዢያና የፖላር አካባቢዎች ናቸው፤ ይህ መረጃ በጽሑፍ ሰፍሮ የሚገኝ ቢሆንም ለማንኛውም መጠንቀቅ ይበጃል፡፡
ከተነደፍን በኋላ ምን ማድረግ አለብን?
አብዛኛውን ጊዜ በእባቦች የሚደርስብን ጥቃት በመርዛማ እባቦች የሚፈፀም አይደለም፡፡ በዓለማችን ላይ ከሚደርሱ በእባብ የመነደፍ አደጋዎች እንድ አራተኛ የሚሆኑት ናቸው የመርዛማ እባብ ሰለባ የሚሆኑት፡፡ በሚገጥሙን ችግሮች ላይ በተጨማሪ፣ በመርዛማ እባቦች መነደፍ ሁኔታዎችን ከቁጥጥር ውጪ ሊያደርግብን ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ያልጠበቅናቸው አሳዛኝ ታሪኮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በእባብ በምንነደፍበት ወቅት ወሳኙ ነገር የመርዙን ፈጣን የመዛመት ሂደት ዘገም ለማድረግ መሞከር ነው፡፡ የተነደፍንበት አካባቢን በጨርቅ በማሰርና ቦታውን በስለት በመብጣት መርዙን በመጭመቅ የተቻለንን ያክል ለማውጣት መሞከር አለብን፡፡ መርዛማ ባልሆኑ እባቦች የተነከስን ከሆነ፣ የተነከስንበት አካባቢ ሊያመረቅዝ ስለሚችል ተገቢውን የአንቲባዮቲክ ሕክምናና የንፅህና ክትትል በማድረግ ቁስለቱን ማዳን አለብን፡፡ በመርዛማ እባቦች መነደፍ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው መርዙ የሚያጠቃው የነርቭ ስርዓታችንን ብቻ ሳይሆን የደም ዝውውርንና  ምግብ ለመፍጨት የሚያገለግሉትን ኢንዛይሞች ጭምር መሆኑ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ተገቢው ሕክምና በጊዜው ካልተሰጠ መርዙ፣ ሕብረህዋሶችን ወይም ቲሹዎችን የመግደል አቅም አለው፡፡ በሕክምና የሚሰጠው መፍትሄ እንደጉዳቱ መጠን፣ የተነደፈውና የተመረዘው አካላችንን እስከመቁረጥ የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፤ ከዚህ አልፎ ተርፎም እስከ ሞት ሊያደርሰን ይችላል፡፡ በእባብ ከተነደፍን በኋላ የፍርሃት እና የመረበሽ ስሜቶች እንዲሁም እንቅስቃሴ ማብዛት መርዙ በሰውነታችን ውስጥ በፍጥነት እንዲዛመት በማድረግ ችግሩን ያባብሳሉ፤ ስለዚህ ከተነደፍን በኋላ በተቻለን መጠን መረጋጋት አለብን፡፡ በተነደፍን በ30 ደቂቃ ውስጥ ራሳችንን የመሳት እድሉ የሰፋ በመሆኑ ቅድመ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ በማንኛውም እባብ ከተነደፍን በኋላ ሕክምና ማድረግ ከመጀመራችን በፊት እድሉን ካገኘን እባቡ መርዛማ ነው አይደለም የሚለውን ለመለየት መሞከር አለብን፡፡
የሕክምና እርዳታ
  • የተነደፈውን ሰው እንዳይንቀሳቀስ ማስተኛት፣
  • በጨርቅ ወይም በገመድ ከተነደፈው ቦታ በላይ አጥብቆ ማሰር፣
  • እብጠት ወዲያው ስለሚፈጠር ሰዓት፣ የጣት ቀለበት እና የእጅ አምባር የመሳሰሉትን ቁሶች በፍጥነት ማውለቅ፣
  • የተነደፈውን ቦታ ማፅዳት፣
  • ንፁህ አየር እንዲያገኝ መርዳት፤ ራሱን ከሳተም የአፍ-ለ-አፍ ትንፋሽ የመጀመሪያ እርዳታ ማድረግ፣
  • የተነደፈውን ቦታ በስለት በመብጣት እየጨመቁ ፈሰሹ እዲወጣ ማድረግ፣
  • የተነከሰው ሰው በተቻለ ፍጥነት የማርከሻ(Antivenin) መርፌ እንዲወጋ መደረግ አለበት፤ ይህን ማድረግ ካልቻልን የሞት አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡
በመርዛማ እባብ የተነደፈ ሰው ከሚከተሉት ነገሮች መቆጠብ አለበት
  • ከአልኮል እና ሲጋራ፣
  • ህመምን ሊቀንሱ ከሚችሉ እንደ ሞርፊን ያሉ መድኃኒቶች፣
  • አይንን በእጅ ከመነካካት(አነስተኛ መጠን ያለው መርዝ ወደ ዓይናችን ከገባ፣ አይናችንን ሊያጠፋ ይችላል፡፡)
  • የተነደፈውን አካባቢ እብጠት ከማሻሸት መቆጠብ አለበት፡፡
ማስታወሻ(በጥንቃቄ ሊከወን የሚገባ)  በቅርበት ንም አይነት የሕክምና እርዳታ ማግኘት የማንችል ከሆነ፣ በስለት መርዙ የገባበትን ቀዳዳ በማስፋትና አፋችንን ተጠቅመን በመምጠጥ፣ ከዛም በመትፋት እስከ 30% የሚሆነውን መርዝ ማውጣት እንችላለን፡፡ ይህንን እርዳታ ካደረግን በኋላ በፍጥነት አፋችንን በውኃ በተደጋጋሚማጠብና መጉመጥመጥ አለብን፤ ዚህ ዘዴ ለመጠቀም በአፋችን ውስጥ ምንም አይነት ቁስለት አለመኖሩን ማረጋገጥ አለብን፡፡
 ከዚህ በላይ በተመለከትናቸው ዘዴዎች መርዙን ካወጣን በኋላ፡-
  • ቁስለቱ እንዳያመረቅዝ ማፅዳትና አየር እንዲያገኝ ማድረግ፣
  • ቁስለቱን በንፁህ ጨርቅ መሸፈን፣
  • ተጎጂው ብዙ ፈሳሽ እንዲጠጣ ማድረግ አለብን፡፡
መላ፡- ቁስለቶችን ለማፅዳት ውኃ ማግኘት የማንችል ከሆነ ሽንታችንን ልንጠቀም እንችላለን፡፡
ለመርዛማ እባብ ንድፊያ የሚሰጠው የማርከሻ መድኃኒት እንደዝርያቸው ወይም እንደሚያጠቁት የሰውነት ክፍል የሚለያይ ነው፤ ለምሳሌ የአንድ እባብ መርዝ እክል የሚፈጥረው በደም ላይ፣ በልብ ላይ፣ በነርቭ ሥርዓት ላይ፣ በጡንቻና በሌሎች አካላት ላይ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም በማርከሻ መድኃኒት መፍትሔ ለማግኘት፣ ምን ዓይነት የእባብ ዝርያ እንደነደፈን ማወቅ አለብን፡፡ ከንድፊያ በኋላ የሚፈጠርን ቁስለት እንደማንኛውም ቁስለት እንዳያመረቅዝ ተንከባክቦ ማዳን ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ከባድ ጠባሳ ሊተው አልፎ ተርፎም የአካል መቆረጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡
ምንጭ:- www.survival101.info

Comments

Popular posts from this blog

ጤናአዳም ብዙ የጤና በረከቶች እንዳሉት ሁሉ መጠኑ ሲበዛ ፅንስ እስከማስወረድ የሚደርስ አደገኛነት እንዳለው ያውቃሉ?

የስኳር በሽታ እንዴት ይፈጠራል? መቆጣጠሪያ መንገዱስ እንዴት ነው?