የስኳር በሽታ እንዴት ይፈጠራል? መቆጣጠሪያ መንገዱስ እንዴት ነው?

የስኳር በሽታ፣ ጉሉኮስ፣ ግላይኮጅን፣ ግሉካጎንና ኢንሱሊን ያላቸው ግንኙነት
ግሉኮስ(glucose)
ግሉኮስ ቀለል ያለ የስኳር ውቅር ነው፤ አቻ የሞለኪል ቀመሩ (C6H12O6) ሲሆን በእንስሳት ደም ውስጥ የሚዘዋወር ለሕዋሶች አስፈላጊ የሆነ የኃይል ምንጭ ነው፤ ግሉኮስን የሚሰሩት እፅዋት ናቸው፤ እፅዋት ውኃ እና ካርቦን ዳይኦክሳይድን ከፀሐይ ብርሃን ጋር በማስተፃመር ነው የሚያመርቱት፤ ግሉኮስ በእፅዋት ውስጥ በስታርች( starch) መልክ የሚቀመጥ ሲሆን በእንስሳት ውስጥ ደግሞ ግላይኮጅን( glycogen) በሚባል ግን’ብ መልክ ይቀመጣል፡፡
ኢንሱሊን ምንድነው? በሰውነታችን ውስጥ የሚሰራው ስራ ምንድነው?
ምግብ ከተመገብን በኋላ፣ ከምግቡ የምናገኘው ግሉኮስ(glucose) በትንሹ አንጀት በኩል አድርጎ ወደ ደም ይቀላቀላል፤ ይህም በመሆኑ ምግብ ከተመገብን በኋላ የግሉኮስ መጠን በደማችን ውስጥ ይጨምራል፤ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ሕዋሶች በደም ውስጥ የሚገኘውን ግሉኮስ ለተለያዩ ስራቸው እንደ ኃይል ይጠቀሙታል፤ ይህ ሂደት በደም ውስጥ የሚገኝ የግሉኮስ መጠን ክምችት እንዲቀንስ ያደርጋል፤ ሕዋሶቻችን የሚጠበቅባቸውን ተግባራት በሚገባ ለማከናወን በደም ውስጥ የሚገኘው የግሉኮስ መጠን ሳይዋዥቅ በሆነ መጠን ላይ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቆይ ያስፈልጋል፤ ሚዛኑን ጠብቆ በሆነ ልኬት ላይ እንዲቆይ ግን የሆነ መቆጣጠሪያ መንገድ ያስፈልገዋል፤ አለዚያ ጉሉኮስ በደም ውስጥ ወይ በጣም መብዛት ወይም ማነስ ያጋጥማል፡፡ኢንሱሊን የዚህን ቁጥጥር ስራ የሚሰራ ቅመም ወይም ሆርሞን ነው፡፡
ኢንሱሊን
ጉበት
ጉበት በደም ውስጥ የሚገኘውን የግሉኮስ መጠን ለመቆጣጠር የሚረዳ ሚና አለው፤ ከጉበት በተጨማሪም ቆሽታችን(pancreas) በዚህ ተግባር ላይ ዋና ተሳታፊ ነው፤ የጉበት ሕዋሶች በደም ውስጥ የሚገኘውን ግሉኮስ በመምጠጥ ይዘው ግላይኮጅን(glycogen) ወደሚባል ግን’ብ በመቀየር ያስቀምጡታል፤ ይህ ግላይኮጅን(glycogen) ባስፈለገ ጊዜ በፍጥነት ወደ ግሉኮስ(glucose) በመሰባበር ወደ ደም መመለስ የሚችል ነው፤  ይህ ሂደት ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ቁርስ፣ ምሳ እና እራት
በየእለቱ የምንመገብበት ሰዓት ጥለት(pattern) አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ነው፤ ነገር ግን የምንመገበው ምግብ የካርቦሃይድሬት ይዘት መጠን ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይም በየእለቱ፣ በስራም ሆነ በሌላ መንገድ የምናደርገው እንቅስቃሴ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይነት አለው፤ እነኝህ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ኃይል የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በሁለት የተለያዩ ቀናት የሚኖረን አመጋገብና እንቅስቃሴ አንድ ዓይነት ባይሆንም ተቀራራቢ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም ብዙ ምግብ የምንበላበት ወይም ብዙ እንቅስቃሴዎች የምናደርግበትም ቀን ሊኖር ይችላል፤ ወይም ደግሞ ምግብ የማንበላበት እና ራሳችንን ከእንቅስቃሴ የምንገድብበት ጊዜም አለ፤ በመሆኑም በነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጠር የውስጠ አካላችን የኃይል ምንዛሪ ሚዛን መጠበቅ ወይም ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፤ ይህም ሲባል ግሉኮስ(glucose) ወደ ግላይኮጅን(glycogen)፤ ግላይኮጅን(glycogen) ወደ ግሉኮስ(glucose) የሚቀየርበት ሂደት ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፤ ገንባ-አፍርስ የሚለውን ስራ የሚሰሩት የጉበት ሕዋሶች እንደመሆናቸው መጠን በሰውነታችን ውስጥ የጉሉኮስ መጠን መቼ ከፍ -ዝቅ እያለ እንደሆነ ከሰውነታችን ከሆነ ቦታ መረጃው ሊደርሳቸው ይገባል፡፡ ይህንን መረጃ በመለካት ለጉበት ሕዋሶች የሚያደርሱት በቆሽታችን ውስጥ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሕዋሶች ናቸው፡፡
ምግብ ከተመገብን በኋላ፣ ከምግቡ የምናገኘው ግሉኮስ(glucose) በትንሹ አንጀት በኩል አድርጎ ወደ ደም ይቀላቀላል
ጤነኛ የሚባለው በደማችን ውስጥ መኖር ያለበት የግሉኮስ መጠን (0.1%) ነው፤ በመሆኑም በቆሽታችን ውስጥ የሚገኙ ሕዋሶች ይህንን ሁኔታ ይከታተላሉ፤ የግሉኮስ መጠን በደም ውስጥ ከሚገባው በላይ ከፍ ሲል ኢንሱሊን(Insulin) የተባለውን ቅመም ወይም ሆርሞን በመልቀቅ ጉበት በሰውነት ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የግሉኮስ መጠን ወደ ግላይኮጅን(glycogen) ለውጦ እንዲያስቀምጥ ይነግሩታል፤ በመሆኑም በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን ይቀንሳል፤ በተመሳሳዩም የግሉኮስ መጠን በደም ውስጥ ከሚገባው መጠን በታች እየቀነሰ ሲመጣ(<0.1%) በቆሽታችን ውስጥ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሕዋሶች ሁኔታውን ስለሚከታተሉ ግሉካጎን(glucagon) የተባለውን ሌላኛውን ቅመም ወይም ሆርሞን በመልቀቅ በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እየወረደ ስለሆነ አከማችተህ የያዝከውን  ግላይኮጅን(glycogen) ወደ ግሉኮስ(glucose) በመቀየር በደም ውስጥ እያነሰ የመጣውን የጉሉኮስ መጠን ጨምር ብለው ለጉበት ይነግሩታል፤ ይህ በመሆኑም ሕዋሶች ለስራቸው በቀጥታ እንደኃይል ምንጭ የሚያገለግላቸው የግሉኮስ(glucose) መጠን ልኬቱ  በሰውነት ውስጥ ተጠብቆ ይቆያል፡፡

ኢንሱሊን የሕዋሶች በር ተከፍቶ ጉሉኮስ ወደ ሕዋሶቹ ዘልቆ እንዲገባ ያደርጋል፤ ልክ እንደቁልፍ ማለት ነው

የስኳር ሕመምተኞች የሚገጥማቸው ምንድነው?
አንዳንድ ሰዎች ቆሽታቸው ላይ በሚያጋጥም ችግር በቂ የሆነ ኢንሱሊን አያመርቱም፤ ይህ ሁኔታ በዘር በመተላለፍ ወይም በእርጅና  ምክንያት ሊያጋጥም ይችላል፤ በመሆኑም ሰውነታቸው በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን የግሉኮስ(glucose) ልኬት መጠን መቆጣር ይሳነዋል፤ ይህም በመሆኑ ስኳር(diabetes) የተባለው በሽታ እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል፤ እንግዲህ አንድ ሰው በህይወት ለመቆየት በደሙ ውስጥ የሚገኘው የግሉኮስ(glucose) መጠን 0.1% ላይ መቆየት እንዳለበት አይተናል፤ አለበለዚያ ሕዋሶቻችን ከጥቅም ውጪ የመሆን ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል፤ በተለይ ደግሞ የአንጎል ሕዋሶች በደም ውስጥ የሚገኘው የግሉኮስ(glucose) መጠን በጥቂቱም ሲጨምር መቋቋም አይችሉም፤ የጉሉኮስ መጠንን ለመቆጣጠር ትክክለኛ የኢንሱሊን መጠን የማያገኙ ከሆነ በፍጥነት ራስን መሳትና ሞት ሊያጋጥም ይችላል፡፡
ስኳር የሚድን በሽታ አይደለም፤ ነገር ግን መቆጣጠር ይቻላል፤ የበሽታው ምክንያት በደም ውስጥ የግሉኮስ(glucose) መጠን መጨመር በመሆኑ አንደኛው መንገድ የምንመገበው ምግብ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ነው፤ ይህም ሲባል እንደካርቦሃይድሬት ያሉ ስኳር የሚበዛቸው ምግቦች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነው፤ የስኳር ታማሚ ሆነን ሁኔታውን ምግብ ላይ ቁጥጥር በማድረግ የማይሳካልን ከሆነ ደግሞ ሰው ሰራሽ የሆነ የኢንሱሊን ቅመም በመወጋት ሁኔታውን መቆጣጠር ነው፡፡
ኢንሱሊን ሁሌ በመርፌ ከመወጋት ሌላ አማራጭ የለም ወይ?
ኢንሱሊን ሁሌ በመርፌ ከመወጋት ሌላ አማራጭ የለም ወይ?
የኢንሱሊን ውቅር ፕሮቲን ነው፤ ይህ ሁኔታ ችግር ነው፤ ምክንያቱም በአፍ ሊወሰድ አይችልም፤ በአፍ ከተወሰደ ከሌሎች ከምንመገባቸው ምግቦች ጋር በከርስ ውስጥ አብሮ እንደማንኛውም ፕሮቲን በመሰባበር ይፈጫል፤ በዚህም ምክንያት ኢንሱሊን የግድ በመርፌ መወሰድ አለበት፡፡ መረጃው ከጣመዎ ለወዳጆችዎም ያጋሩ!
ምንጭ:- www.survival101.info

Comments

Popular posts from this blog

በዓለም ላይ ከሚገኙት ወደ 3000 የሚጠጉ የእባብ ዝርያዎች 600 የሚሆኑት መርዛማ ናቸው፤ የተነደፍነው በመርዛማ እባቦች መሆኑን እንዴት እንለያለን? ምንስ ማድረግ አለብን?

ጤናአዳም ብዙ የጤና በረከቶች እንዳሉት ሁሉ መጠኑ ሲበዛ ፅንስ እስከማስወረድ የሚደርስ አደገኛነት እንዳለው ያውቃሉ?